8 ስለማንኛውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበው ካህን ቈዳውን ለራሱ ይውሰድ።
9 በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ፣ በመቀቀያ ወይም በምጣድ የበሰለ ማንኛውም የእህል ቊርባን ለሚያቀርበው ካህን ይሰጥ።
10 ማናቸውም በዘይት የተለወሰ ወይም ደረቅ የእህል ቊርባን ለአሮን ልጆች ሁሉ እኩል ይሰጥ።
11 “ ‘አንድ ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሊከተለው የሚገባው ሥርዐት ይህ ነው፦
12 “ ‘መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ለምስጋና መግለጫ ከሆነ፣ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋር ያለ እርሾ የተጋገረና በዘይት የተለወሰ ኅብስት እርሾ ሳይገባበት በሥቡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ በሚገባ ታሽቶ በዘይት የተለወሰም የላመ ዱቄት ኅብስት አብሮ ያቅርብ።
13 ለምስጋና ከሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ጋር በእርሾ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ።
14 ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየ ቊርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ።