ዘኁልቍ 23:13-19 NASV

13 ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደ ምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ እዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው።

14 ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

15 በለዓምም ባላቅን፣ “እርሱን ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ” አለው።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) በለዓምን ተገናኘው፤ በአፉም መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

17 እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋር በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ ባላቅም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን አለ?” ሲል ጠየቀው።

18 ከዚያም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤“ባላቅ ሆይ ተነሣ፤ አድምጠኝ፤የሴፎር ልጅ ሆይ ስማኝ፤

19 ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰው አይደለም፤ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤ተናግሮ አያደርገውምን?ተስፋ ሰጥቶስ አይፈጽመውምን?