3 በዓሉንም በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በተወሰነው ሕግና ሥርዐት መሠረት ሁሉ አክብሩ።”
4 ስለዚህ ሙሴ ፋሲካን እንዲያከብሩ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤
5 እነርሱም በመጀመሪያው ወር፣ በዐሥራ አራተኛውም ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካ አደረጉ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉንም አደረጉ።
6 አንዳንዶቹ ግን የሰው ሬሳ በመንካታቸው በሥርዐቱ መሠረት ረክሰው ስለ ነበር በዚያን ዕለት የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህም በዚያኑ ዕለት ወደ ሙሴና ወደ አሮን መጥተው፣
7 ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት።
8 ሙሴም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ የሚያዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው።
9 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤