10 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ።
11 ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።
12 የኔር ልጅ አበኔር፣ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ።
13 እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኵሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ አንዱ ወገን በኵሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኵሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ።
14 ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጒልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው።ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ።
15 ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ።
16 ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር” ተባለ።