1 የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ትዕማር የምትባል ቈንጆ እኅት ነበረችው፤ እርሷንም የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት።
2 አምኖን እኅቱን ትዕማርን ከማፍቀሩ የተነሣ እስኪታመም ድረስ ተጨነቀ፤ ድንግል ስለሆነች እርሷን ማግኘት የማይቻል ሆኖ አግኝቶታልና።
3 አምኖን ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ነው። ኢዮናዳብ እጅግ ተንኰለኛ ሰው ነበር።
4 አምኖንንም፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳበትን ምክንያት ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው።አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው።
5 ኢዮናዳብም፣ “እንግዲያው ‘ታምሜአለሁ’ ብለህ ዐልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ብትሰጠኝ ደስ ይለኛል፤ መብሉንም እዚሁ አጠገቤ ሆና እያየሁ አዘጋጅታ በእጇ እንድታጐርሰኝ እባክህ ፍቀድልኝ ብለህ ንገረው” አለው።
6 ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፣ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፣ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው።
7 ዳዊትም፣ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” በማለት ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤተ መንግሥቱ ላከ።
8 ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ አዘጋጅታ ጋገረችው፤
9 ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም።አምኖንም፣ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ያለውም ሰው ሁሉ ትቶት ወጣ።
10 ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች።
11 ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት።
12 እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ።
13 እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።”
14 እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፣ በግድ አስነወራት፤ ከእርሷም ጋር ተኛ።
15 ከዚያም አምኖን እጅግ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት የበለጠ ጠላት። አምኖንም፣ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት።
16 እርሷም፣ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፣ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን አልተቀበላትም፤
17 በግል የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ፣ “ይህቺን ሴት ከዚህ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው።
18 ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ ጌጠኛ የሆነና በዚያን ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን ዐይነት ልብስ ለብሳ ነበር።
19 ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነሰነሰች፤ ጌጠኛ ልብሷን ቀደደች፤ ከዚያም እጇን በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች።
20 ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ያ ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለ ሆነ፤ ነገሩን በልብሽ አትያዢው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች።
21 ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤
22 አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አንዳች ቃል አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አምኖን እኅቱን ትዕማርን ስላ ስነወራት ጠልቶት ነበር።
23 ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ድንበር አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ በዚህን ጊዜ የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት ጋበዛቸው።
24 አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፤ ባሪያህ በጎቹን እየሸለተ ነው፤ ታዲያ ንጉሡና ሹማምቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው።
25 ንጉሡም፣ “ልጄ ሆይ፣ ሁላችንም መሄድ የለብንም፤ ሸክም እንሆንብሃለን” ሲል መለሰለት። አቤሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ መሄድ አልፈለገም፤ ነገር ግን መርቆ አሰናበተው።
26 አቤሴሎምም፣ “እንግዲያውስ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው።ንጉሡም፣ “አብሮአችሁ የሚሄደው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
27 ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፣ አምኖንና ሌሎቹ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ አደረገ።
28 አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፣ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ ከዚያም እኔ አምኖንን፣ ‘ምቱት’ ስላችሁ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ” ብሎ አዘዛቸው።
29 የአቤሴሎምም አገልጋዮች ጌታቸው ያዘዛቸውን በአምኖን ላይ ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ።
30 እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው።
31 ንጉሡም ተነሥቶ ቆመ፤ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።
32 የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የንጉሡን ልጆች በሙሉ እንደ ፈጇቸው አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ቈርጦ የተነሣበት ጒዳይ ስለ ሆነ፣ የሞተው አምኖን ብቻ ነው።
33 እንግዲህ የሞተው አምኖን ብቻ ስለ ሆነ፣ ‘የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተገደሉ’ ተብሎ የተነገረውን ንጉሥ ጌታዬ ማመን የለበትም።”
34 አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ከእርሱ በስተ ምዕራብ ካለው መንገድ ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ቍልቍል ሲወርዱ አየ፤ ዘብ ጠባቂውም ሄዶ ለንጉሡ፣ “ከበስተ ሖሮናይም አቅጣጫ በኰረብታው ጥግ ላይ ሰዎች ቍልቍል ሲወርዱ አያለሁ” ብሎ ነገረው።
35 ኢዮናዳብም ዳዊትን፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኖአል” አለው።
36 ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ እጅግ አለቀሱ።
37 አቤሴሎም ኰብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፤ ነገር ግን ዳዊት ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር።
38 አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ጌሹር ከሄደ በኋላ፣ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ።
39 ንጉሥ ዳዊት በልጁ በአምኖን ሞት ከደረሰበት ሐዘን ከተጽናና በኋላ፣ ወደ አቤሴሎም ለመሄድ መንፈሱ ተነሣሣ።