2 ሳሙኤል
ምዕራፎች 3
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ።
2ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤የበኵር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣
3ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣ ሦስተኛው፣ ተልማይ ከተባለው ከጌሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣
4አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣
5ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።