1 እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦልም እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ዘመረ፤
2 እንዲህም አለ፤“እግዚአብሔር ዐለቴ ዐምባዬና ታዳጊዬ ነው፤
3 አምላኬ፣ የምጠጋበት ዐለቴ፣ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ ነው።እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊያና አዳኜ ነው፤ከኀይለኞች ሰዎች ታድነኛለህ።
4 ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርንእጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
5 “የሞት ማዕበል ከበበኝ፤የጥፋትም ጐርፍ አሰጠመኝ።
6 የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞትም ወጥመድ ተጋረጠብኝ።
7 በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ወደ አምላኬም ጮኽሁ።እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ።
8 “ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤የሰማያትም መሠረቶች ተናጉ፤እርሱ ተቈጥቶአልና ራዱ።
9 ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ከውስጡም ፍሙ ጋለ።
10 ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
11 በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤በነፋስም ክንፍ መጠቀ።
12 ጨለማው በዙሪያው እንዲከበው፣ጥቅጥቅ ያለውም የሰማይ ዝናም ደመና እንዲሰውረው አደረገ።
13 በእርሱ ፊት ካለው ብርሃን፣የመብረቅ ብልጭታ ወጣ።
14 እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤የልዑልም ድምፅ አስተጋባ።
15 ፍላጻውን ሰድዶ ጠላቶቹን በተናቸው፤መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው።
16 ከእግዚአብሔር ተግሣጽ፣ ከአፍንጫውከሚወጣው፣ ከእስትንፋሱ ቍጣ የተነሣ፣የባሕር ሸለቆዎች ታዩ፤ የምድርመሠረቶችም ተገለጡ።
17 “ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ።
18 ከብርቱ ጠላቶቼ፣ከማልቋቋማቸውም ባለጋሮቼ ታደገኝ።
19 በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፈኝ።
20 ሰፊ ወደ ሆነ ስፍራ አወጣኝ፤በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ።
21 “እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤እንደ እጄም ንጹሕነት ብድራትን ከፈለኝ፤
22 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ከአምላኬም ዘወር ብዬ ክፉ ነገር አላደረግሁም።
23 ሕጉ ሁሉ በፊቴ ነው፤ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም።
24 በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።
25 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፣በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ።
26 “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን፣ለቅን ሰው አንተም ቅን መሆንህን ታሳያለህ።
27 ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ።
28 አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል።
29 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
30 በአንተ ርዳታ በጠላት ሰራዊት ላይ ወደፊት ገፍቼ እሄዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥሩን እዘላለሁ።
31 “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤
32 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን አለና፤ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው?
33 ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው።
34 እግሮቼን እንደ ብሆር እግር ያበረታል፤በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል።
35 እጆቼን ለጦርነት ያሰለጥናል፤ክንዶቼም የናስ ቀስት ይገትራሉ።
36 የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል።
37 እርምጃዬን አሰፋህ፤እግሮቼም አልተሰነካከሉም።
38 “ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤እስኪደመሰሱም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም።
39 ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ ተመልሰውም መቆም አልቻሉም፤ከእግሬም ሥር ወድቀዋል።
40 ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፣ተቃዋሚዎቼንም ከእግሬ ሥር አንበረከካቸው።
41 ጠላቶቼ ፊታቸውን አዙረው እንዲሸሹ አደረግሃቸው።ባላንጣዎቼንም ደመሰስኋቸው።
42 ለርዳታ ጮኹ፤ ያዳናቸው ግን አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግንአልመለሰላቸውም።
43 በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አድቅቄ ፈጨዃቸው፤በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም።
44 “በሕዝቤ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ።የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤
45 ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል።
46 ባዕዳን ፈሩ፤ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ።
47 “እግዚአብሔር ሕያው ነው፤ ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤የድነቴ ዐለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል።
48 የሚበቀልልኝ አምላክ፣መንግሥታትንም ከሥሬ የሚያስገዛልኝ እርሱ ነው፤
49 እርሱ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ ያወጣኛል።አንተ ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ።
50 ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤በመንግሥታት መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ።
51 ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፣ለዘላለም የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳየዋል።”