2 ሳሙኤል 20 NASV

ሳቤዔ በዳዊት ላይ ዐመፀ

1 በዚህ ጊዜ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የተባለ አንድ ምናምንቴ ብንያማዊ በዚያ ነበረ፤ እርሱም መለከት ነፍቶ እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እኛ ከዳዊት ድርሻ የለንም፤ ከእሴይም ልጅ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፤ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ!”

2 ስለዚህ የእስራኤል ሰው ሁሉ ዳዊትን ከድቶ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተለ። የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንሥቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው ሳይ ለዩ አብረውት ሄዱ።

3 ዳዊት ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በተመለሰ ጊዜ፤ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ትቶአቸው የሄደውን ዐሥሩን ቁባቶቹን ወሰደ፤ በአንድ ቤትም ውስጥ እንዲጠበቁ አደረገ። ቀለብ ሰጣቸው፤ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ አልገባም ነበር፤ እነርሱም እስከ ሞቱበት ጊዜ ድረስ መበለት ሆነው፣ ለብቻቸው ተገልለው ተቀመጡ።

4 ከዚያም ንጉሡ አሜሳይን፣ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ፣ ወደ እኔ እንዲመጡ ጥራልኝ፤ አንተ ራስህም ተገኝ” አለው።

5 አሜሳይ ይሁዳን ለመጥራት ሄደ፤ ነገር ግን ንጉሡ ከወሰነው ጊዜ በላይ ቈየ።

6 ዳዊትም አቢሳን፣ “ከአቤሴሎም ይልቅ አሁን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ የበለጠ ጒዳት ሊያደርስብን ስለ ሆነ የጌታህን ሰዎች ይዘህ አሳደው፤ ያለዚያ የተመሸገ ከተማ አግኝቶ ያመልጠናል” አለው።

7 ስለዚህ የኢዮአብ ሰዎች፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ሌሎች ኀያላን ጦረኞች በሙሉ በአቢሳ አዛዥነት ወጡ፤ ከኢየሩሳሌም የወጡትም የቢክሪ ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ነበር።

8 በገባዖን ከታላቁ ቋጥኝ አጠገብ ሳሉ፣ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፤ ኢዮአብ የጦር ሜዳ ልብሱን ለብሶ ሰይፉን ከሰገባው በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ ወደ ፊት ራመድ እንዳለም ሰይፉ ከሰገባው ወጥቶ ወደቀ።

9 ኢዮአብም አሜሳይን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እንደምንድን ነህ?” አለው፤ ከዚያም አሜሳይን የሚስም መስሎ በቀኝ እጁ ጢሙን ያዘው።

10 አሜሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ሰይፍ መኖሩን ልብ ስላላለ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ስለዚህ ኢዮአብ ሰይፉን ሆዱ ላይ ሻጠበት፤ አንጀቱም መሬት ላይ ተዘረገፈ፤ ከዚያም ኢዮአብ መድገም ሳያስፈልገው፣ አሜሳይ በዚያው ሞተ። ከዚህ በኋላ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ፣ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ማሳደድ ጀመሩ።

11 በአሜሳይ ሬሳ አጠገብ ከቆሙት ከኢዮአብ ሰዎች አንዱ፤ “ኢዮአብን የሚወድ፣ የዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል!” አለ።

12 በዚህን ጊዜ የአሜሳይ ሬሳ በደም ተጨማልቆ በመንገዱ መካከል ወድቆ ነበር፤ በዚያ የሚያልፈው ሰራዊት ሁሉ መቆሙን ያ ሰው አየ፤ ወደ ሬሳው የደረሰው ሰራዊት ሁሉ መቆሙን በተረዳ ጊዜም፣ የአሜሳይን ሬሳ ከመንገድ ወደ ዕርሻ ፈቀቅ አድርጎ ልብስ ጣል አደረገበት።

13 የአሜሳይ ሬሳ ከመንገድ ላይ ከተነሣ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ኢዮአብን ተከትሎ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ሊያሳድድ ሄደ።

14 ሳቤዔም በእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ዐልፎ ወደ አቤል ቤትማዓካና ወደ መላው የቢክሪያውያን ግዛት መጣ፤ የቢክሪ ሰዎችም ተሰብስበው ተከተሉት።

15 ከኢዮአብ ጋር ያለውም ሰራዊት መጥቶ ሳቤዔን በአቤል ቤትመዓካ በኩል ከበበው፤ በስተ ውጭም እስከ ከተማዪቱ ግንብ ጫፍ ድረስ ዙሪያውን የዐፈር ድልድል ሠሩ፤ ግንቡን ለመናድ በኀይል በሚደበድቡበት ጊዜ፣

16 አንዲት ብልኅ ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “ስሙ! ስሙ! ለኢዮአብ የምነግረው ነገር ስላለ ወደዚህ እንዲመጣ ንገሩት” አለቻቸው።

17 ኢዮአብ ወደ እርሷ ሄደ፤ እርሷም፣ “ኢዮአብ አንተ ነህ?’ ስትል ጠየቀችው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰላት።እርሷም፣ “እንግዲህ አገልጋይህ የምትለውን አድምጥ” አለችው።እርሱም፣ “እሺ፣ አደምጣለሁ” አላት።

18 ከዚያ በመቀጠልም እንዲህ አለች፤ “በቀድሞው ጊዜ ሰዎች፣ ‘ምክርን ከአቤል ጠይቁ’ ይሉ ነበር፤ ታዲያ እንዳሉትም ይፈጸም ነበር፤

19 በእስራኤል ሰላማዊና ታማኝ ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዷ እኔ ነኝ፤ አንተ በእስራኤል እናት የሆነችውን ከተማ ለማጥፋት ትሻለህ፤ የእግዚአብሔርን ርስት ለመዋጥ የፈለግኸው ለምንድን ነው?”

20 ኢዮአብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይህስ ከእኔ ይራቅ! መዋጡና ማጥፋቱ አሁንም ከእኔ ይራቅ!

21 ነገሩስ እንዲህ አይደለም፤ የኰረብታማው የኤፍሬሙ አገር ሰው፣ የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ እጁን በንጉሡ በዳዊት ላይ አንሥቶአል፤ እናንተ ይህን ሰው ብቻ ስጡኝ እንጂ እኔ ከተማዪቱን ትቼ እሄዳለሁ” አላት።ሴቲቱም ኢዮአብን፣ “የሰውየው ራስ ተቈርጦ በግንቡ ላይ ይወረወርልሃል” አለችው።

22 ከዚህም በኋላ ሴቲቱ ብልኅነት የተሞላበት ምክሯን ይዛ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሳቤዔን ራስ ቈርጠው ለኢዮአብ ወረወሩለት፤ ስለዚህ ኢዮአብ መለከቱን ነፋ፤ ሰዎቹም ከከተማዪቱ ርቀው በየአቅጣጫው ተበታተኑ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው ሄዱ፤ ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

23 ኢዮአብ በእስራኤል ሰራዊት ሁሉ ላይ የበላይ ሆነ፤ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ደግሞ በከሊታውያንና በፈሊያታውያን ላይ አለቃ ሆነ።

24 አዶኒራም በግዳጅ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ሰዎች አለቃ ሆነ፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ ታሪክ ጸሓፊ ሆነ፤

25 ሱሳ ጸሓፊ፣ ሳዶቅና አብያታር ካህናት ነበሩ፤

26 እንዲሁም የኢያዕር ሰው ዒራስ የዳዊት አማካሪ ነበር።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24