1 ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ።
2 እርሱና አብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በታቦቱ ላይ ባለው ኪሩቤል ላይ በተቀመጠው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ወደ በአል ሄዱ።
3 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፣ በኰረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአሚናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ሲሆኑ፣
4 የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፣ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር።
5 ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጽናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር።
6 ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእስራኤልን ታቦት ያዘ።
7 ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ።
8 የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን ስለ ሰበረው፣ ዳዊት ተከፋ፤ አዘነም፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል።
9 ዳዊት በዚያን ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “የእግዚአብሔር ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ።
10 ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት አብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው።
11 የእግዚአብሔርም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰዉን ሁሉ ባረከ።
12 በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተ ሰውና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው።
13 እነዚያ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት ርምጃ በሄዱ ቍጥር፣ አንድ በሬና አንድ የሰባ ጥጃ ይሠዋ ነበር።
14 ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኀይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይጨፍር ነበር።
15 እንዲህ ባለ ሁኔታም ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት ሆይ! እያሉና ቀንደ መለከቱን እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ።
16 የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ፣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው።
17 ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው፣ ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አግብተው በተዘጋጀለት ስፍራ አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ።
18 ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ሕዝቡን በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ባረከ።
19 የእስራኤል ወገን ለሆነው ለሕዝቡ ሁሉ፣ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጀራ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ሄደ።
20 ዳዊት ቤተ ሰዉን ለመመረቅ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ፣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ልትቀበለው ወጥታ፣ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቍቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” አለችው።
21 ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “አዎን ከአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ አስበልጦ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ገዥ አድርጎ በመረጠኝ በእግዚአብሔር ፊት አሸብሽቤአለሁ፤ አሁንም አሸበሽባለሁ።
22 እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፤ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ።”
23 የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር።