1 አኪጦፌልም፣ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰው መርጬ፣ በዛሬዪቱ ሌሊት አባትህን አሳድደዋለሁ፤
2 በደከመውና ዐቅም ባነሰው ጊዜም አደጋ እጥልበታለሁ፤ ሽብር እለቅበታለሁ፤ ከዚያም አብሮት ያለው ሕዝብ ሁሉ ትቶት ይሸሻል፤ ንጉሡን ብቻ እመታዋለሁ፣
3 ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፣ አንተ የምትፈልገው የአንድ ሰው ብቻ መሞት ሁሉም እንዲመለሱ ያደርጋል። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይኖራል።”
4 ምክሩም አቤሴሎምንና አብረውት የነበሩትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ።
5 አቤሴሎም ግን፣ “እስቲ ደግሞ አርካዊውን ኩሲን ጥሩትና የሚለውን እንስማ” አለ።
6 ኩሲ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፣ “አኪጦፌል ይህን ምክር አቅርቦአል፤ ታዲያ እርሱ ያለውን እናድርግ? ካልሆነም እስቲ የአንተን ሐሳብ ንገረን” አለው።
7 ኩሲም አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “አኪጦፌል የሰጠው ምክር በዚህ ጊዜ የሚያዋጣ አይደለም፤
8 አባትህና ሰዎቹ የማይበገሩ ተዋጊዎችና ግልገሎቿም እንደ ተነጠቁባት የዱር ድብ አስፈሪ መሆናቸውን አንተም ታውቃለህ፤ በተጨማሪም አባትህ በቂ ልምድ ያለው ነው፤ ሌሊቱን ከሰራዊቱ ጋር አያድርም፤
9 እነሆ፤ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል። እርሱ ቀድሞ አደጋ በመጣል ከሰዎችህ ጥቂት ቢሞቱ ይህን የሰማ ሁሉ፣ ‘አቤሴሎምን የተከተለው ሰራዊት አለቀ’ ብሎ ያወራል።
10 አባትህ ታላቅ ጦረኛ፣ አብረውት ያሉትም ጀግኖች መሆናቸውን እስራኤል ሁሉ ስለሚያውቅ፣ ልቡ እንደ አንበሳ ልብ ነው የተባለው ደፋሩ ወታደር እንኳ በፍርሀት ይርዳል።
11 “እንግዲህ እኔ የምመክርህ ይህ ነው፤ ቍጥሩ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛው፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው እስራኤል ሁሉ ወዳንተ ይሰብሰብና አንተው ራስህ ወደ ጦርነቱ ምራው፤
12 ከዚያም እርሱ እገባበት ቦታ ሁሉ ገብተን አደጋ እንጥልበታለን፣ ጤዛ በመሬት ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ሰዎቹ አንድ እንኳ አይተርፉም፤
13 ከአንዲቱ ከተማ ቢገባ፣ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይቀር ድረስ፣ ከተማዪቱን ወደ ሸለቆ ስበን እንከታታለን።”
14 አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፣ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የኩሲ ምክር ይሻላል” አሉ፤ እግዚአብሔር በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት ሲል መልካም የነበረው የአኪጦፌል ምክር ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎአልና።
15 ኩሲም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲህ አላቸው፤ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክሮአቸው ነበር፤ እኔ ግን እንዲህ እንዲህ አድርጉ ብዬ መክሬአቸዋለሁ።
16 አሁንም በፍጥነት ላኩና፣ ‘በምድረ በዳው ባለው የወንዙ መሻገሪያ እንዳታድር፤ ሳትዘገይ ፈጥነህ መሻገር አለብህ፤ ያለዚያ ግን ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ትዋጣላችሁ’ ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት።”
17 በዚህ ጊዜ ዮናታንና አኪማአስ ወደ ከተማዪቱ ከገቡ ስለሚታዩ በዓይንሮጌል ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይ ወደዚያ እየሄደች በምትነግራቸው ጊዜ፣ እነርሱ ደግሞ ይህንኑ ወስደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር።
18 ሆኖም አንድ ወጣት አያቸውና ለአቤሴሎም ነገረው፤ ስለዚህ ሁለቱም በፍጥነት ተነሥተው በብራቂም ወደሚገኝ ወደ አንድ ሰው ቤት ሄዱ፤ ሰውየው በግቢው ውስጥ ጒድጓድ ስለ ነበረው ወደዚያው ወረዱ።
19 ሚስቱም በጒድጓዱ አፍ ላይ የስጥ ማስጫ ዘርግታ እህል አሰጣች፤ ማንም ይህን አላወቀም ነበር።
20 የአቤሴሎም ሰዎች እዚያ ቤት ወደ ሴቲቱ ዘንድ መጥተው፣ “አኪማአስና ዮናታን የት አሉ?” ብለው ጠየቁ።ሴቲቱም፣ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” ብላ መለሰችላቸው፤ እነርሱም ፈልገው ስላጧቸው፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
21 ሰዎቹ ከሄዱ በኋላ እነዚህ ሁለቱ ከጒድጓዱ ወጥተው ሄዱ፤ ለንጉሥ ዳዊትም፣ “አኪጦፌል በአንተ ላይ እንዲህ እንዲህ ብሎ ስለ መከረብህ ተነሥተህ በፍጥነት ወንዙን ተሻገር” አሉት።
22 ስለዚህ ዳዊትና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ተነሥቶ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም።
23 አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉት ባየ ጊዜ፣ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወደሚገኝበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም መልክ መልክ ካስያዘ በኋላ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በአባቱ መቃብር ተቀበረ።
24 አቤሴሎም ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ሲሻገር፣ ዳዊት ግን መሃናይም ደርሶ ነበር።
25 አቤሴሎምም በኢዮአብ ምትክ አሜሳይን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ አሜሳይ የእስማኤላዊው የዮቴር ልጅ ነበረ፤ ዮቴርም የኢዮአብን እናት፣ የጽሩያን እኅት፣ የናዖስን ልጅ አቢግያን አግብቶ ነበር።
26 እስራኤላውያንና አቤሴሎም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ።
27 ዳዊት መሃናይም ሲደርስ፣ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፣ የናዖስ ልጅ ሾቢ፣ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ
28 መተኛ ምንጣፎች፣ ወጭቶችና የሸክላ ዕቃዎች ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ስንዴና ገብስ፣ ዱቄትና የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላና ምስር፣
29 ማር፣ እርጎ፣ በጎችና የላም አይብ እንዲበሉ ለዳዊትና ለሕዝቡ አመጡላቸው፤ ይህን ያደረጉትም፣ “ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቦአል፤ ደክሞአል፤ ተጠምቶአል” በማለት ነው።