2 ሳሙኤል
ምዕራፎች 19
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው።
2ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ።
3በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ።
4ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ።
5ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍ ረሃቸዋል።
6የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ።
7በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።”
8ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የቤታቸው ሸሽተው ነበር።