2 ሳሙኤል

ምዕራፎች 7

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ተስፋ

1ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣ 2ነቢዩን ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። 3ናታንም፣ “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው። 4በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤ 5“ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤ 6እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። 7ከእስራኤላውያን ሁሉ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፣ “ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?” ያልሁት አለን? 8“አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ 9በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ 10የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፣ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከዚህ በፊት እንደሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቍነውም፤ 11ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ሁሉ ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ። “ ‘እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤ 12ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀ ላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 13ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። 14አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል ቢፈጽም ግን ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ። 15ምሕረቴን ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ሁሉ ከእርሱ አላርቅም። 16ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ” 17ናታንም የዚህን የጠቅላላውን ራእይ ቃል በሙሉ፣ ለዳዊት ነገረው።

የዳዊት ጸሎት

18ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤“ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 19ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው? 20“ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና! 21ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል። 22ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 23ለራሱ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ሊታደገው፣ እግዚአብሔር በፊቱ እንደሄደለት ሕዝብ፣ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና አማልክቶቻቸውን ከፊቱ አሳዶ ታላቅና አስፈሪ ታምራት እንዳደረገለትና ከግብፅም እንደ ተቤዠው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ማን አለ? 24ሕዝብህን እስራኤልን ለዘላለሙ ያንተው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆነኸዋል። 25“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም ጠብቅለት፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ 26ስለዚህ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሆናል፤ ሰዎችም፣ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ። የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። 27“አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ‘እኔ ለአንተ ቤት እሠራልሃለሁ’ ብለህ ይህን ለባሪያህ ገልጸህለታል። ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ በልቡ ደፈረ። 28ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም የታመነ ነው፤ ይህንንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል፤ 29በፊትህ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር፣ አሁንም የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ። ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አንተው ራስህ ተናግረሃል፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረካል።