11 የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣
12 ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ሰዎች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር።
13 ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ።
14 የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
15 እንደ ገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ በዚያም ደከመው።
16 ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢብኖብ የተባለ፣ የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ፤ እርሱም ዳዊትን ለመግደል አሰበ።
17 የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፣ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት።