2 ሳሙኤል 3:8-14 NASV

8 አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለተቈጣ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ የምወግን የውሻ ጭንቅላት ነኝን? ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ ታማኝነቴን እስከ ዛሬ ድረስ አላጓደልሁም፤ አንተንም አሳልፌ ለዳዊት አልሰጠሁም፤ አሁን ግን አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን?

9 እግዚአብሔር ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ እዳር እንዲደርስ ሳላደርግ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግበት፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤

10 የማለለትም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አውጥቶ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት የሰጠው ተስፋ ነው።”

11 ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።

12 ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ተስማማ፤ እነሆ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ አንዲመለስ እኔ እረዳሃለሁ” ብለው ለዳዊት እንዲነግሩለት መልክተኞች ላከ።

13 ዳዊትም፣ “ይሁን እሺ፣ ከአንተ ጋር ስምምነቱን አደርጋለሁ፣ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ ያለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ።

14 ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት።