ሉቃስ 13:11-17 NASV

11 በዚያም የድካም መንፈስ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አካለ ስንኩል ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ከመጒበጧ የተነሣ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር።

12 ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፣ “አንቺ ሴት፤ ከሕመምሽ ነጻ ወጥ ተሻል” አላት፤

13 እጁንም በላይዋ ጫነ፤ እርሷም ወዲያው ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።

14 የምኵራቡ አለቃ ግን፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን፣ “ሥራ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላ ቸው።

15 ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እናንት ግብዞች፤ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው በሬውን ወይም አህያውን በሰንበት ቀን ከማደሪያው ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣ ይወስደው የለምን?

16 ታዲያ፣ ይህች ሴት የአብርሃም ልጅ ሆና ሳለች ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትኖር፣ ከዚህ እስራት በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?”

17 ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ ዐፈሩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን እርሱ ባደረገው ድንቅ ሥራ ሁሉ ደስ አላቸው።