1 ነገሥት 21:15-21 NASV

15 ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው።

16 አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።

17 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

18 “ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል።

19 እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ? ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”

20 አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ።

21 ‘እነሆ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ዘርህን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ እያንዳንዱን የአክዓብን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ከእስራኤል እጠርጋለሁ።