1 እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በአራት መቶ ሰማንያ ዓመት፣ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።
2 ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ነበር።
3 በቤተ መቅደሱ ዋነኛ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ወርዱ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ሁሉ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወደ ውጭ የወጣ ነበር።
4 ለቤተ መቅደሱም ባለ ዐይነ ርግብ መስኮቶች አበጀ።
5 በዋናው ቤተ መቅደስና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግድግዳ ዙሪያ ልዩ ክፍሎች ያሉት ተቀጥላ ግንብ ሠራ።
6 የምድር ቤቱ ወርድ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ፎቅ ስድስት ክንድ፣ የሦስተኛው ፎቅ ሰባት ክንድ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ዘልቆ እንዳይገባም፣ ከቤተ መቅደሱ ግንብ ውጭ ዙሪያውን እርከኖች አደረገ።
7 ቤተ መቅደሱ የተሠራው እዚያው ድንጋዩ ተቈፍሮ ከወጣበት ቦታ በተዘጋጀ ድንጋይ በመሆኑ የመራጃ፣ የመሮ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ በቤተ መቅደሱ አካባቢ አልተሰማም ነበር።