1 ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ በመመለስ፣ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቈየ።
2 በሦስተኛውም ቀን የተቀደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም፣ ወደ መሬት ለጥ ብሎ በአክብሮት እጅ ነሣ።
3 ዳዊትም፣ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር ሸሽቼ መምጣቴ ነው” በማለት መለሰለት።
4 ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ።
5 ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው።
6 ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤