1 ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት፣ በጸደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን ከንጉሡ ሰዎችና ከመላው የእስራኤል ሰራዊት ጋር አዘመተው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ረባት የተባለችውንም ከተማ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።
2 አንድ ቀን ማታ፣ ዳዊት ከዐልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፣ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች።
3 ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ አጠያየቀ። ሰውየውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ።
4 ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች።
5 ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፣ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት።