1 እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ።
2 ባለ ጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤
3 ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች።
4 ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።
5 ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!
6 እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለ ማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።”
7 ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤