2 ሳሙኤል

ምዕራፎች 12:3-9

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

3ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። 4ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው። 5ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! 6እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለ ማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” 7ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ 8የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። 9ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው።