4 የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።
5 ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት።እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤
6 እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው።
7 እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።”
8 ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጒዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።
9 ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች።
10 ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት።