2 ሳሙኤል 15:29-35 NASV

29 ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ።

30 ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር።

31 በዚህ ጊዜ፣ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ።

32 ዳዊትም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደ ሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ ሲደርስ፣ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ።

33 ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤

34 ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ።

35 ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተው ጋር ይሆኑ የለምን? ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ንገራቸው።