3 ከዚያም ንጉሡ፣ “የጌታህ ልጅ የት ነው?” ሲል ጠየቀው።ሲባም፣ “ ‘የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል’ ብሎ ስለሚያስብ፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል” አለው።
4 ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው።ሲባም፣ “በታላቅ ትሕትና በግንባሬ ተደፍቼ እጅ እነሣለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው።
5 ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ፣ ከሳኦል ቤተ ሰብ ነገድ የሆነ አንድ ሰው ብቅ አለ፤ እርሱም የጌራ ልጅ ሳሚ ነው፤ እየተራገመም ወጣ።
6 የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊት ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳ፣ በዳዊትና በሹማምቱ ላይ ሁሉ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር።
7 ሳሚም እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ክፉ ሰው፤
8 መንግሥቱን የወሰድክበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”
9 ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፤ “ይህ የሞተ ውሻ፣ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሻገርና ራሱን ልቍረጠው” አለ።