4 ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው።ሲባም፣ “በታላቅ ትሕትና በግንባሬ ተደፍቼ እጅ እነሣለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው።
5 ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ፣ ከሳኦል ቤተ ሰብ ነገድ የሆነ አንድ ሰው ብቅ አለ፤ እርሱም የጌራ ልጅ ሳሚ ነው፤ እየተራገመም ወጣ።
6 የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊት ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳ፣ በዳዊትና በሹማምቱ ላይ ሁሉ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር።
7 ሳሚም እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ክፉ ሰው፤
8 መንግሥቱን የወሰድክበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”
9 ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፤ “ይህ የሞተ ውሻ፣ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሻገርና ራሱን ልቍረጠው” አለ።
10 ንጉሡ ግን፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች እናንተንና እኔን የሚያገናኘን ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፣ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው።