2 ሳሙኤል 18:10-16 NASV

10 አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው።

11 ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፣ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መተህ መሬት ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፣ ዐሥር ሰቅል ጥሬ ብርና የጀግና ሰው ቀበቶም እሸልምህ ነበር” አለው።

12 ሰውየው ግን እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፣ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጒዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’ ብሎ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለ ሆነ፣ አንድ ሺህ ሰቅል ጥሬ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፣ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም።

13 በሌላ በኩል ደግሞ በነፍሴ ቈርጬ ሕይወቱን ባጠፋው ኖሮ፣ ከንጉሡ ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ፣ አንተም ራስህ አትቀርበኝም ነበር” ብሎ መለሰለት።

14 ኢዮአብም፣ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ፣ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው።

15 እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት።

16 ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ መለከት ነፍቶ ስለ ከለከላቸው፣ ሰራዊቱ እስራኤልን ማሳደዱን አቆመ።