14 ኢዮአብም፣ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ፣ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው።
15 እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት።
16 ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ መለከት ነፍቶ ስለ ከለከላቸው፣ ሰራዊቱ እስራኤልን ማሳደዱን አቆመ።
17 አቤሴሎምን ጫካ ወስደው በትልቅ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት፤ በላዩም ትልልቅ ድንጋይ ከመሩበት። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ የቤታቸው ሸሹ።
18 አቤሴሎም፣ “ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም” በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ ስለ ነበር፣ እስከ ዛሬ ድረስ የአቤሴሎም ሐውልት ተብሎ ይጠራል።
19 በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ፣ “እግዚአብሔር ጠላቶቹን የተበቀለለት መሆኑን ሮጬ ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው” አለ።
20 ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፣ ዛሬ ሳይሆን፣ የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው።