2 ሳሙኤል 18:20-26 NASV

20 ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፣ ዛሬ ሳይሆን፣ የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው።

21 ከዚያም ኢዮአብ ለኢትዮጵያዊው፣ “ሂድና ያየኸውን ለንጉሡ ንገር” አለው፤ ኢትዮጵያዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ።

22 የሳዶቅ ልጅ አኪማአስም እንደ ገና ኢዮአብን፣ “የመጣው ይምጣ፤ እባክህ ኢትዮጵያዊውን ተከትየው ልሩጥ” አለው።ኢዮአብ ግን፣ “ልጄ ሆይ፣ መሄድ ለምን አስፈለገህ? ሽልማት የሚያሰጥህ ምን የምሥራች ይዘህ ነው?” ብሎ መለሰለት።

23 አኪማአስም፣ “የመጣው ይምጣ፤ መሄድ እፈልጋለሁ” አለ።ስለዚህም ኢዮአብ፣ “እንግዲያውማ ሩጥ!” አለው። ከዚያም አኪማአስ በሜዳው መንገድ ሮጦ ኢትዮጵያዊውን ቀድሞት ሄደ።

24 ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ሳለ፣ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ሲመለከት አንድ ሰው ብቻውን ሲሮጥ አየ።

25 ጠባቂውም ተጣራና ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ንጉሡም፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ መጣ።

26 ከዚያም ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ አይቶ፣ ዘበኛውን ተጣራና፣ “እነሆ ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለ።ንጉሡም፣ “ይኸኛውም መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ።