2 ሳሙኤል 18:9-15 NASV

9 በዚህ ጊዜ አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ጋር ድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ይሄድ ስለ ነበር፣ በቅሎዋ ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው ትልቅ ወርካ ሥር በምታልፍበት ጊዜ፣ የአቤሴሎም ራስ በዛፉ ቅርንጫፍ ተያዘ፤ የተቀመጠበትም በቅሎ በሥሩ ስታልፍ፣ እርሱ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠልጥሎ ቀረ።

10 አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው።

11 ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፣ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መተህ መሬት ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፣ ዐሥር ሰቅል ጥሬ ብርና የጀግና ሰው ቀበቶም እሸልምህ ነበር” አለው።

12 ሰውየው ግን እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፣ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጒዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’ ብሎ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለ ሆነ፣ አንድ ሺህ ሰቅል ጥሬ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፣ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም።

13 በሌላ በኩል ደግሞ በነፍሴ ቈርጬ ሕይወቱን ባጠፋው ኖሮ፣ ከንጉሡ ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ፣ አንተም ራስህ አትቀርበኝም ነበር” ብሎ መለሰለት።

14 ኢዮአብም፣ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ፣ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው።

15 እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት።