2 ሳሙኤል 6:1-7 NASV

1 ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ።

2 እርሱና አብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በታቦቱ ላይ ባለው ኪሩቤል ላይ በተቀመጠው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ወደ በአል ሄዱ።

3 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፣ በኰረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአሚናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ሲሆኑ፣

4 የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፣ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር።

5 ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጽናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር።

6 ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእስራኤልን ታቦት ያዘ።

7 ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ።