መሳፍንት 12:4-10 NASV

4 ከዚያም ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋር ተዋጋ። ኤፍሬማውያን ገለዓዳውያንን፣ “እናንተ ገለዓዳውያን ከኤፍሬምና ከምናሴ የከዳችሁ ናችሁ” ይሏቸው ስለ ነበር በብርቱ መቷቸው።

5 ገለዓዳውያን ወደ ኤፍሬም የሚያሻግሩትን የዮርዳኖስን መልካዎች ያዙ፤ ታድያ አምልጦ የሚሸሽ አንድ ኤፍሬማዊ ለመሻገር በሚጠይቃቸው ጊዜ፣ የገለዓድ ሰዎች “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ ያም ሰው፣ “አይደለሁም” ብሎ ከመለሰላቸው፣

6 እስቲ “ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ ታዲያ ቃሉን በትክክል ማለት ሳይችል ቀርቶ “ሲቦሊት” ካለ ይዘው እዚያው እመልካው ላይ ይገድሉታል፤ በዚያ ጊዜም አርባ ሁለት ሺህ ኤፍሬማውያን ተገደሉ።

7 ዮፍታሔ በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።

8 ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ።

9 እርሱም ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ሴቶች ልጆቹንም ከጐሣው ውጭ ለሆኑ ሰዎች ዳራቸው፤ ጐሣው ውጭ የሆኑ ሠላሳ ልጃገረዶች አምጥቶ ከወዶች ልጆቹ ጋር አጋባቸው። ኢብጻን በእስራኤል ላይ ሰባት ዓመት ፈራጅ ሆነ።

10 ኢብጻን ሞተ፤ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።