መሳፍንት 13:4-10 NASV

4 እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገርም አትብዪ፤

5 ምክንያቱም ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል።”

6 ከዚያም ሴቲቱ ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ የሚመስልና እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር። ከየት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤

7 ነገር ግን፣ ‘ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኵስ ነገር አትብዪ፤ ልጁም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና’ ብሎኛል።”

8 ከዚያም ማኑሄ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ አንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

9 እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ አብሮአት አልነበረም።

10 እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።