22 ከሚካ ቤት ጥቂት ራቅ እንዳሉም፣ የሚካ ጎረቤቶች ለርዳታ ተጠርተው ተሰበሰቡ፤ የዳን ሰዎችንም ተከታትለው ደረሱባቸው።
23 ከበሰተኋላቸው ሆነው ሲጮኹባቸውም፣ የዳን ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው ሚካን፣ “ሰዎችህን ለውጊያ አሰባስበህ መምጣትህ ምን ሆንህና ነው?” አሉት።
24 እርሱም፣ “እንዴት፣ ‘ምን ሆንህ’ ብላችሁ ትጠይቁኛላችሁ? የሠራኋቸውን አማልክቴንና ካህኔን ወስዳችሁ ሄዳችኋል፤ ምን የቀረኝ ነገር አለ?” አላቸው።
25 የዳን ሰዎች፣ “አትሟገተን፤ ያለዚያ የተቈጡ ሰዎች ጒዳት ላይ ይጥሉሃል፤ አንተም ቤተ ሰብህም ሕይወታችሁን ታጣላችሁ” አሉት።
26 የዳን ሰዎች ይህን ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም የማይችላቸው መሆኑን በማየት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27 ከዚያም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወስደው ወደ ላይሽ በመሄድ፣ በሰላምና ያለ ስጋት ይኖር የነበረውን ሕዝብ በሰይፍ መቱት፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሏት።
28 የሚኖሩት ከሲዶና በጣም ርቀው ስለ ነበርና ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸው የሚታደጋቸው አንድም አልነበረም፤ ከተማዪቱም የምትገኘው በቤትሮዓብ አጠገብ ነበረ።የዳንም ሰዎች ከተማዪቱን እንደ ገና ሠርተው መኖሪያቸው አደረጓት።