መሳፍንት 19:23-29 NASV

23 የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።

24 እነሆ ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቊባት አሉ፤ እነርሱን አሁኑኑ ላውጣላችሁና አስነውሯቸው፤ ያሻችሁንም አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙበት።”

25 ሆኖም ሰዎቹ ሊሰሙት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ሌዋዊው ቁባቱን ወደ ውጭ አወጣላቸው፤ ሰዎቹም አመነዘሩባት፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲፈራረቁባት አድረው ጐሕ ሲቀድ ለቀቋት።

26 በነጋም ጊዜ ሴቲቱ ጌታዋ ወዳለበት ቤት ተመልሳ ሄደች። ደጃፉ ላይ ወድቃ ፀሓይ እስክትወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች።

27 ጌታዋ በጠዋት ተነሥቶ በሩን በመክፈት መንገዱን ለመቀጠል ሲወጣ፣ ቁባቱ እጅዋን ከደጃፉ መድረክ ላይ እንደ ዘረጋች ከቤቱ በራፍ ላይ ተዘርራ ወድቃ አገኛት።

28 ሌዋዊውም፣ “በዪ ተነሺና እንሂድ” አላት፤ ነገር ግን መልስ አልነበረም። ከዚያም በአህያው ላይ ከጫናት በኋላ ወደ ቤቱ ጒዞውን ቀጠለ።

29 ቤቱ እንደ ደረሰም ቢላዋ አንሥቶ ቁባቱን ዐሥራ ሁለት ቦታ በመቈራረጥ ወደ እስራኤል ምድር ሁሉ ሰደደ።