መሳፍንት 20:33-39 NASV

33 የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ ካለው ቦታ ወጣ።

34 ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር።

35 እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ።

36 ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ።በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።

37 ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላዪቱን ከተማ በሰይፍ መቱ።

38 የእስራኤል ሰዎች ያሸመቀው ጦር በከተማዪቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳይ፤

39 እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ተስማሙ።ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፣ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፣ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ።