መሳፍንት 21:6-12 NASV

6 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤

7 ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በእግዚአብሔር ስለ ማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?”

8 ከዚያም፣ “ከእስራኤል ነገዶች ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን ነው” ሲሉ ጠየቁ፤ ታዲያ ከኢያቢስ ገለዓድ አንድም ሰው ለጉባኤው ወደ ሰፈሩ አለመምጣቱን ተረዱ፤

9 ሕዝቡን ሲቈጥሩም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች አንድም ሰው አልነበረምና።

10 ስለዚህ ዐሥራ ሁለት ሺህ ተዋጊዎች ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሄደው በእዚያ የሚኖሩትን በሙሉ ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጭምር በሰይፍ እንዲፈጇቸው ጉባኤው መመሪያ ሰጥቶ ላካቸው።

11 እነርሱም፣ “እንግዲህ የምታደርጉት ይህ ነው፤ ወንዱን በሙሉ እንዲሁም ድንግል ያልሆኑትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ” አሏቸው።

12 በኢያቢስ ገለዓድ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ወንድ ያልደረ ሰባቸው አራት መቶ ደናግል አገኙ፤ በከነዓን ምድር በሴሎ ወደ ሚገኘውም ሰፈር አመጧቸው።