1 በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፣ እግዚአብሔር ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው፤
2 ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው፤
3 እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፣ ከነዓናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ።
4 እነዚህ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኵል ለቀደሙ አባቶቻቸው የሰጠውን ትእዛዛት ማክበር አለማክበራቸውን ለማወቅ መፈተኛ እንዲሆኑ እዚያው የቀሩ ነበሩ።
5 ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ።
6 እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።