1 እንደ ገና እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ገዟቸው።
2 እስራኤላውያን የምድያማውያን ኀይል ስለ በረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፣ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ።
3 እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር።
4 እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህል ዘር አያስተርፉም፣ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር።
5 ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቍጠር አዳጋች ሲሆን፣ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር።