1 የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን ይዞ እንደ ደመሰሳት፣ እንደዚሁም በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ማድረጉን፣ የገባዖን ሰዎችም ከእስራኤል ጋር የሰላም ውል አድርገው በአጠገባቸው መኖራቸውን ሰማ፤
2 በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።
3 ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የየርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣
4 “ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው።
5 ከዚያም አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት።