ኢያሱ 10:2-8 NASV

2 በዚህም እርሱና ሕዝቡ ደነገጡ፤ ምክንያቱም ገባዖን እንደ ነገሥታቱ ከተማ ሁሉ ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥ፣ ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።

3 ስለዚህ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ሆሃም ወደተባለው የኬብሮን ንጉሥ ጲርአም ወደተባለው የየርሙት ንጉሥ፣ ያፊዓ ወደተባለው የለኪሶ ንጉሥና ዳቤር ወደተባለው የዔግሎን ንጉሥ በመላክ፣

4 “ወደዚህ ወጥታችሁ አግዙኝ፤ ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላምን መሥርታለችና ገባዖንን እንምታ” አላቸው።

5 ከዚያም አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ማለት የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የዔግሎን ንጉሥ ያላቸውን አስተባብረው፣ ሰራዊታቸውንም ሁሉ ይዘው በመውጣት ገባዖንን ወጓት።

6 የገባዖንም ሰዎች በጌልገላ ወደ ሰፈረው ወደ ኢያሱ፣ “በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው ተሰልፈውብናል፤ እኛን ባሮችህን አትተወን፤ ርዳን፤ ፈጥነህ በመድረስም አድነን” ሲሉ ላኩበት።

7 ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ።

8 እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው።