ኢያሱ 2:10-16 NASV

10 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል።

11 ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና።

12 እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤

13 የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን እንዲሁም የእነርሱ የሆነውን ነፍስ ሁሉ እንድታተርፉልኝ፤ ከሞትም አድኑን።”

14 ሰዎቹም፣ “የእናንተን ሞት ለእኛ ያድርገው! እኛ የምናደርገውን ሁሉ ካልተናገራችሁ፣ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ፣ በጎነትና ታማኝነት እናሳይሻለን” አሏት።

15 መኖሪያ ቤቷ የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ስለ ነበር፣ ሰዎቹን በመስኮት አሾልካ በገመድ አወረደቻቸው።

16 እርሷም፣ “የሚከታተሏችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ፣ ወደ ኰረብታዎቹ ሂዱ፤ እነርሱ እስኪመለሱም ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተሸሸጉ፤ ከዚያ በኋላ መንገዳችሁን ትቀጥላላችሁ” አለቻቸው።