ኢያሱ 5:3-9 NASV

3 ስለዚህ ኢያሱ የባልጩት መቍረጫ አዘጋጅቶ በጊብዓዝ ዓረሎት በተባለ ስፍራ እስራኤላውያንን ገረዛቸው።

4 እንግዲህ ኢያሱ እስራኤላውያንን የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ዕድሜያቸው መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ ሳሉ በምድረ በዳ ሞቱ።

5 ከዚያ የወጡት ሰዎች ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ በጒዞ ላይ ሳሉ የተወለዱት ግን በሙሉ አልተገረዙም ነበር።

6 ግብፅን ለቀው በወጡ ጊዜ መሣሪያ ለመያዝ የደረሱ ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፣ እነርሱ ሞተው እስኪያልቁ ድረስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይንከራተቱ ነበር። እግዚአብሔር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው ቃል የገባላቸውን ያችን ማርና ወተት የምታፈስ ምድር እንደማያዩአት ምሎአልና።

7 ስለዚህ በእነርሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሣ፤ እንግዲህ ኢያሱ የገረዛቸው እነዚህን ነበር፤ በጒዞ ላይ ሳሉ ባለመገረዛቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩና።

8 ሕዝቡ ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቍስሉ እስኪሽር ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቈዩ።

9 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነሆ፤ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባል ያለሁ” አለው፤ ከዚህም የተነሣ የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተባለ።