ኢያሱ 5:7-13 NASV

7 ስለዚህ በእነርሱ ምትክ ወንዶች ልጆቻቸውን አስነሣ፤ እንግዲህ ኢያሱ የገረዛቸው እነዚህን ነበር፤ በጒዞ ላይ ሳሉ ባለመገረዛቸው ከነሸለፈታቸው ነበሩና።

8 ሕዝቡ ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቍስሉ እስኪሽር ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቈዩ።

9 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነሆ፤ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባል ያለሁ” አለው፤ ከዚህም የተነሣ የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተባለ።

10 እስራኤላውያን በኢያሪኮ ሜዳ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ፣ ወሩ በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የፋሲካን በዓል አከበሩ።

11 ከፋሲካም በኋላ በዚያኑ ዕለት የምድሪቱን ፍሬ ማለት ያልቦካ ቂጣና የተጠበሰ እሸት በሉ።

12 የምድሪቱ ፍሬ በበሉበት ቀንተ መናው መውረዱ ቀረ፤ ከዚያ በኋላ ለእስራኤላውያን መና አልወረደላቸውም፤ ነገር ግን በዚያኑ ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።

13 ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ከፊቱ ቆሞ አየ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው።