25 እጄ ባገኘችው ሀብት፣በባለጠግነቴም ብዛት ደስ ብሎኝ ከሆነ፣
26 የፀሓይን ድምቀት አይቼ፣ወይም የጨረቃን አካሄድ ግርማ ተመልክቼ፣
27 ልቤ በስውር ተታልሎ፣ስለ ክብራቸው አፌ እጄን ስሞ ከሆነ፣
28 ለልዑል እግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኔ ነውና፣ይህም ደግሞ የሚያስቀጣኝ በደል በሆነ ነበር።
29 “በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ፣በደረሰበትም መከራ ሐሤት አድርጌ እንደሆነ፣
30 እኔ ግን በነፍሱ ላይ ክፉ እንዲመጣ በመራገም፣አንደበቴን ለኀጢአት ከቶ አሳልፌ አልሰጠሁም።
31 የቤቴ ሰዎች፣ ‘ከኢዮብ ከብት ሥጋ አስቈርጦ፣ያልጠገበ ማን ነው’ ብለው ካልሆነ፣