ዘሌዋውያን 10:1-6 NASV

1 የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረቡ።

2 ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ሞቱ።

3 ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ)፦‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።”አሮንም ዝም አለ።

4 ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው።

5 እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።

6 ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቊጣ እንዳይመጣ ጠጒራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ።