ዘሌዋውያን 17:1-7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለአሮንና ለልጆቹ፣ ለእስራኤላውያንም ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤

3 ማንኛውም እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈር ውጭ በሬ፣ በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፣

4 በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፣ ያ ሰው በከንቱ ደም እንዳፈሰሰ ይቈጠራል፤ ደም በማፍሰሱም ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ።

5 እስራኤላውያን የሚሠዉትን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡበት ምክንያት ከዚሁ የተነሣ ነው። ይህንም ካህኑ ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥተው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት በማድረግ ያቅርቡ።

6 ካህኑም ደሙን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ላይ ይርጭ፤ ሥቡንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ሽታ እንዲሆን ያቃጥል።

7 ከዚህ በፊት ላመነዘሩባቸው አጋንንት ከእንግዲህ ወዲህ ማንኛውንም መሥዋዕት ሊሠዉ አይገባም። ይህ ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ የዘላለም ሥርዐት ይሁን።’