ዘሌዋውያን 19:15-21 NASV

15 “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በትክክል ፍረድ።

16 “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ፤“ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

17 “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።

18 “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

19 “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤“ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል፤“ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤“ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።

20 “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም።

21 ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያምጣ።