3 የተረፈውም የእህሉ ቊርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው ቊርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።
4 “ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቊርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም ያለ እርሾ በስሱ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን።
5 የእህል ቊርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ከተለወሰ ከላመ ዱቄት ይዘጋጅ።
6 ቈራርሰህ ዘይት አፍስበት፤ ይህ የእህል ቊርባን ነው።
7 የእህል ቊርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ።
8 በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቊርባን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤
9 ከእህሉም ቊርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።