24 አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠው።
25 እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ”
26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
27 “ጥጃ ወይም የበግ ግልገል ወይም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቈይ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ግን ተቀባይነት ያለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ይሆናል።
28 ላምን ከጥጃዋ፣ በግንም ከግልገሏ ጋር በአንድ ቀን አትረዱ።
29 “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት።
30 መሥዋዕቱ በዚያኑ ዕለት ይበላ፤ ለሚቀጥለውም ቀን አታሳድሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።