6 እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
7 ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና።
8 እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
9 “ ‘ካህናት ትእዛዛቴን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
10 “ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
11 ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል።
12 የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም።